ለሀሰተኛ የማህበራዊ ድረ ገጽ አካውንቶች የህግ ማዕቀፍ ወይስ እገዳ
የዓለም አቀፉ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ የሆነው ፌስቡክ ካሉት ከሁለት ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች መካከል በሐሰትና በማመሳሰል የተከፈቱት 270 ሚሊዮን መሆኑን ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። በኢትዮጵያም የፌስቡክ ተጠቃሚ ከሆኑት አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች መካከል በውሸትና በማስመሰል በባለስልጣናት፥ በታዋቂ ሰዎች እንዲሁም በተቋማት ስም የተከፈቱ አካውንቶች እንዳሉና አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆኑ ይገለጻል። የማስመሰል አካውንት ከተከፈተባቸው መካከል ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ እንደሚለው፤ እርሱን በማስመሰል በተከፈተው አካውንት ላይ እንደሚተላለፈው መልዕክት ቢሆን ለህይወቱም ጭምር አስጊ ሁኔታ ይፈጠር ነበር። የብዙ ድርጅቶች ባለቤትና ሁለት ሺ ያህል ሰራተኞችን በስሩ የሚያስተዳድር ሲሆን፤ ይህም ጉዳት የእርሱ ብቻ ሳይሆን የበርካቶችም ጭምር መሆኑን ሊታወቅ ይገባል። የውሸት መልዕክት በእርሱ ስም ማስተላለፍም ትልቅ ወንጀል ነው። ችግሩን ለመፍታት ሲል ወደ ተለያዩ ተቋማት መንቀሳቀሱን የጠቀሰው ሻለቃ ሃይሌ፤ ወደ ፖሊስ ባቀናበት ወቅት ህግ ነውና « የምትጠረጥረው ሰው አለ ?» ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ ደግሞ « የተጨበጠ ነገር አለ ?» መባሉ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማዘጋት እንዳይችል አድርጎታል። በውሸት ከተነገሩበት መካከል በጣም የረበሸው በተለይ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል መካከል በተከሰተው ሁኔታ ኦሮሚያን ወግኖ እንደቆመ ተደርጎ መነገሩ በሌላው ወገን ሊጠላ የሚያስችለው ከመሆኑም በላይ በህይወቱ ላይም አደጋ ሊያስከትልበት ይችል እንደነበር ነው የተናገረው። እርሱ እንደሚናገረው፤ እንዲህ አይነቱ ወንጀል በኢትዮጵያ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ አልተካተተም። ስለዚህ ራሱን የቻለ ህግ ሊቀረፅ ይገባል። ወንጀሉ ከባድ መሆኑን የሚያውቀው ደግ...